ይህ ጥናት በአማርኛ ልቦለዶች ውስጥ የአካል ጉዳተኛነትና የአንስታይነት ተዛናቂነት (Intersectionality) ያለውን መስተጋብር በተመረጡ ሁለት የሴት ደራስያን ሥራዎች ማለትም በጸሐይ መልአኩ “ቢስ ራሔል” እና በእነየ ሺበሺ “የገቦ ፍሬ” ላይ ትኩረት በማድረግ ይፈትሻል። የጥናቱ ዓቢይ ዓላማ አካላዊ ስንነትና ሴትነት በአባታዊ ሥርዓት ውስጥ ተደራርበው እንዴት ለአካል ጉዳተኛነትና ለማኅበራዊ መገለል እንደሚያበቁ መመርመር ነው። ጥናቱ የአካል ጉዳተኛነትን እንደ ማኅበራዊ ሥሪት የሚመለከተውንና የአንስታይ አካል ጉዳተኛነት ንድፈ ሐሳባዊ መሠረቶችን እንደ መተንተኛ መሣሪያ ተጠቅሟል። በጥናቱ የተካተቱት ገጸ ባህርያት ምንም ዓይነት አካላዊ ስንነት ሳይኖርባቸው፣ በማኅበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከትና አሉባልታ ምክንያት ብቻ እንደ አካል ጉዳተኛ ተቆጥረው ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ጫና ደርሶባቸዋል። የምርምሩ ውጤት እንደሚያመላክተው፣ በሁለቱ ልቦለዶች ውስጥ ሴትነትና አካል ጉዳተኛነት ተዛንቀው ሲቀርቡ ጭቆናው የሁለት ችግሮች ድምር ብቻ ሳይሆን ውስብስብና ከድምሩ በላይ የሆነ የማኅበራዊ መገለል ውጤት ሆኖ ተገኝቷል። ገጸ ባህርያቱ ከደረሰባቸው ድርብ ጭቆና ለመውጣትና “ሰው” ሆኖ ለመገኘት የሚያደርጉት ትግል የጥናቱ ማጠቃለያ ሆኖ ቀርቧል። በአጠቃላይ ጥናቱ በሥነ ጽሑፍ ውስጥ የአካል ጉዳተኛ ሴቶችን ምስልና ውክልና በአዲስ እይታ ለመመርመር ጥረት አድርጓል።
Getachew Tesfa Bitew (Mon,) studied this question.