የዚህ ጥናት ዓላማ በደቡብ ወሎ ከስፌትና ከሽመና ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የክልከላ ንግግሮችን መመርመር ነው፡፡ የጥናቱ መነሻ ምክንያቶች በዚህ ረገድ የጥናት ውስንነት፣ ፋይዳዎችና ተግባራዊ ችግሮች መኖር ሲሆን፣ የጥናቱ ቦታዎች በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙት ቃሉ፣ ኮምቦልቻ እና ቦረና ወረዳዎች ናቸው፡፡ የጥናቱ ዓይነት ዓይነታዊ ሲሆን፣ አተያዩ ደግሞ ኢትኖግራፊያዊ ነው፡፡ የመረጃ አቀባዮች የናሙና አወሳሰድ በማህበረሰቡ ዘንድ በሙያው የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው በታላሚ እና በውስጠ አዋቂ ጥቆማ (snowball sampling) የንሞና ዘዴዎች ነው፡፡ በምቹ ሁኔታ መረጃዎችን ለማግኘት ተግዳሮት ሲኖር አመች የናሙና ስልት ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ቀዳማይ መረጃዎች በምልክታ፣ በቃለ መጠይቅ እና በተተኳሪ የቡድን ውይይት ተሰብስበዋል፡፡ እንዲሁም መረጃዎች በተፈጥሮ፣ በቅንብርና በአርቴፊሻል መቼቶች ተሰብስበዋል፡፡ ካልዓይ መረጃዎች ደግሞ የጥናቱን ክፍተት ለማሳየትና ለማናበቢያነት በክለሳ ድርሳንና በጥናቱ ውጤት ማብራሪያ ክፍል ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ መረጃዎቹም ከውስጣዊና ውጫዊ እይታ (Emic & Ethic Perspective) ተተንትነዋል፡፡ የመረጃ ማቅረቡም በገለጻ፣ በሰንጠረዥ፣ በትንተና እና በትርጓሜ ስልቶች ተከናውኗል፡፡ የፋይዳዊነት (Functionalism) ንድፈ ሃሳብ በጥናቱ ለትንተና ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የክልከላዎቹ ንግግሮች በአመዛኙ የሚከወኑት ከመልካምነት እሳቤ በመነጨ ቢሆንም፣ አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው ሁሉ አሉታዊ ሚና እንዳላቸው ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ክልከላዎች የማኅበረሰቡን ነባር ልማድ በማስተማርና በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ይህም ሀገር በቀል ያልሆኑ ልማዶችን በመንቀፍ የማኅበረሰቡ ኃይማኖታዊ ልማድና ወግ ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ በኩል ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ከሥነ ልቦና አኳያ የራስንም ሆነ የማኅበረሰብን እርካታ፣ ከስጋት፣ ከፍርሃትና ከባዕድ ነገር የመጠበቅም ሚና እንዳላቸው ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ በክልከላዎቹ ሴትነትን ዝቅ የሚያደርጉ፣ የጾታ እኩልነትንና የሥራ አካታችነተን የሚነቅፉ ጭብጦች ተንጸባርቀዋል፡፡ ከኢኮኖሚም አኳያ ሰርቶ የመለወጥ ፍልጎትን፣ የሥራ ነጻነትንና ምርጫን በመጋፋት ኢኮኖሚያዊ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸው በአሉታ የሚጠቀሱ ጭብጦች ናቸው፡፡ ክልከላዎቹ የተመሰረቱበት ስልት በንግግሮች፣ በድርጊቶች፣ በአውዶችና በነባራዊ ክስተቶች ነው፡፡ በረከት፣ ወንዳገረድነት፣ ደህንነት፣ ነግ በኔ፣ ማጣትና ክብር በክልከላዎቹ መንሥኤነት ሲጠቀሱ፣ እርግማን፣ ምርቃት፣ ማስጠንቀቂያዎች፣ ማህበራዊ መገለልና ነቀፌታዎች የክልከላ ንግግሮቹና ድርጊቶቹ የማስጠበቂያና የማስቀጠያ ስልቶች እንደሆኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡ እንዲሁም ከክልከላ ድርጊቶች መነሻነት የሚመጡ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ክልክል የሆኑ ድርጊቶችን ማክበርና መፈጸም ተጠቃሽ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ አሉታዊ ሚና ያላቸውን ክልከላዎች ማህበረሰቡን ባማከለ መልኩ በሂደት ወደ አዎንታዊ እሳቤ ሊቀየሩ የሚችሉበትን ስልቶች መፍጠር እንደሚቻል እና በዚህ ረገድ ቀጣይነት ያለው ጥናት ሊካሄድ እንደሚገባ የሚሉ ይሁንታዎች በአጥኚው ቀርበዋል፡፡
ብርሃኑ ቦጋለ ተስፋዬ (Thu,) studied this question.