የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ፣ በግእዝ ቅኔዎችና በሥነ-ቃላዊ ቅርጾች መካከል ያለውን ተራክቦ በመመርመር ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በመሆኑም በግእዝ ቅኔያት ውስጥ እንደቅመም ወይም በማጣፈጫ መልክ እየገቡ ለቅኔው ምሥጢራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሥነ-ቃላዊ ቅርጾችን (ምሳሌያዊ ንግግር፣ እንቆቅልሽ እና ፈሊጥ) ከቅኔው ውስጥ ለይቶ በማውጣት እንዴትና ለምን ዓላማ እንደገቡ ተግባራቸውን ተንትኖ ለማሳየት ተሞክሮበታል፡፡ የጥናቱ ዘዴም በዐይነታዊ የምርምር ዘውግ ስር የተደራጀ ሲሆን መረጃዎቹ በቃለ-መጠይቅና በሰነድ ፍተሻ ተሰብስበዋል፡፡ ቅኔያቱም “ምሳሌያዊ ንግግርን መሠረት ያደረጉ፣ እንቆቅልሻዊ ባሕርይ ያላቸው እና በፈሊጣዊ አነጋገር ላይ የተመሠረቱ የግእዝ ቅኔዎች” በሚሉ ሦስት ዋና ዋና አርእስት ተከፍለው የቀረቡ ሲሆን፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነምግባራዊ በሚሉ ጭብጣዊ መከፋፈያዎች ተደራጅተው፣ ከፋይዳቸው አንጻር ተብራርተውና ተተንትነው ቀርበዋል፡፡ እነዚህም ከሚያስተላልፉት መልእክት አንጻር፣ የማስተማር፣ የማነቃቃት፣ የማሥረጽ፣ የመቆጣጠርና የማምለጫ ተግባራትን ለማከናወን የሚያገለግሉ መኾናቸው በትንተናው ውስጥ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ትንተናው ከጥናቱ ማሕቀፎች (በይነቴክስታዊነትና መዋቅራዊ ተግባራዊነት) ንድፈ ሐሳቦች ጋር እየተገናዘበ ቀርቧል፡፡ በአጭሩ የግእዝ ቅኔ ከላይ የተጠቀሱትን ሥነ-ቃላዊ ቅርጾች እንደ ግብዐት በመጠቀም ለማኅበረሰቡ የሠመረ መልእክት ማስተላለፊያ ኾኖ ግልጋሎት የሚሰጥ መኾኑ ተገልጿል፡፡ ሥነ-ቃልን መነሻ ያደረጉ የግእዝ ቅኔዎች ከሌሎች የቅኔ መንገዶች የሚለዩበት ዋና ጉዳይም “ትውፊት-ተኮር” በመኾናቸው ነው፡፡ ባለቅኔዎች የማኅበረሰቡ አባላት እንደመኾናቸው መጠን፣ ልማዳዊ ስምምነቶችን እና ቃላዊ ጥበቦችን ከሕዝቡ ወስደው ከቅኔያቸው ጋር በተምሳሌትና በንጽጽር አዋሕደው “ይበል” የሚያሰኝ ቅኔ እየፈጠሩ መልሰው ወደ ሕዝቡ የሠመረ መልእክት የሚያስተላልፉባቸው መኾኑን ትንተናው አመላክቷል፡፡ በአጠቃላይ ሥነ-ቃላዊ ቅርጾች፣ ቅኔን ለማመሥጠርና ለመግንባት እንዲሁም ተቀባይነት ያለው መልእክትን ለማስተላለፍ የሚያስችሉ የሐሳብ ማዋቀሪያ ጥበቦች መኾናቸውን የጥናቱ ግኝት አመላክቷል፡፡ በመጨረሻም የግእዝ ቅኔያት ከዚህ በተሻለ መንገድ በየፈርጁ ተደራጅተው ቢጠኑ በርካታ ቁም ነገር እንደሚገኝባቸው ማጠቃለያና አስተያየት በመስጠት ጥናቱን መደምደም ተችሏል፡፡
ተስፋዬ አማረ (Sat,) studied this question.
Synapse has enriched 5 closely related papers on similar clinical questions. Consider them for comparative context: